አርባ ምንጭ ፦ሰኔ 12/2018 ዓ.ም ( አርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች አገልግሎት)፦
በጋሞ ዞን አርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ፍርድ ቤት በ 5 ዓመት ህፃን ላይ የአስገድዶ መድፈር በደል የፈፀመ ወጣት ላይ የ18 ዓመት ጽኑ እስራት ቅጣት ወስኖበታል።
ተከሳሽ ንጋቱ/ቦዬ/በዛብህ/ በሚያዝያ 15 ቀን 2018 ዓ.ም በግምት ከቀኑ 11፡00 ሰዓት አካባቢ በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ በጫኖ ሚሌ ቀበሌ ልዩ ስሙ 02 ሠፈር ተብሎ በሚጠራው ቦታ፣ የግል ተበዳይ የ5 ዓመት ሕፃን ከጓደኞቿ ጋር እየተጫወተች ባለችበት “ቆሎ እሰጥሻለሁ” ብሎ በማታለል ወደ ቤቱ በማስገባት ሆን ብሎ እና አስቦ በፈጸመዉ የግብረ- ሥጋ ድፍረት በደል ወንጀል በወንጀል ሕግ አንቀጽ 627(1) መሠረት ክስ ተመስርቶበታል።
የአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ፍትህ ጽ/ቤት ዓቃቤ ሕግ በተከሳሽ ላይ በቁጥር 2/2018 በቀን 20/2018 ዓ.ም ባቀረበው የወንጀል ክስ መሠረት ተከሳሹ በወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ ቁጥር 128 መሠረት ማንነቱ ተረጋግጦ፣ ክሱ በግልጽ ችሎት በሚገባው ቋንቋ ተነቦለት የተረዳ ቢሆንም ድርጊቱን ሙሉ በሙሉ ክዶ ተከራክሯል።
ዓቃቤ ሕግ በበኩሉ ያስመዘገበውን ጭብጥ ለማስረዳት በቀረበው የሰውና የሕክምና ማስረጃዎችን በማጤን የወረዳው ፍርድ ቤትም የዓቃቤ ሕግን ማስረጃ መርምሮ ተከሳሹ በወ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 142(1) መሠረት እንዲከላከል ብይን ሰጥቷል።
ተከሳሽ የከሳሽ ዐ/ህግ ማስረጃ ቃልን ያስተባብልልኛል ስል ያቀረበው መከላከያ ማስረጃ ቃልን ችሎቱ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ስለወንጀል ማስረጃ የምዘና መርህ በሰጣቸው በርካታ መመሰረታዊ የህግ ትርጉሞችን መሰረት በማድረግ መዝገቡን የመረመረ ሰሆን በዚህም ተከሳሽ ያቀረበው መከላከያ ማስረጃ የከሳሽ ዐ/ህግን የሰውና በህክምና ማስረጃ ማስተባበል ባመቻሉ ተከሳሽን በወ/መ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 149(1)መሰረት የጥፋተኝነት ውሳኔ ሰጥቶበታል።
በመጨረሻም ችሎቱ የጥፋተኝነት ወሳኔን ተከትሎ በግራ ቀኙ በኩል የቅጣት አስተያየት የተቀበለ ስሆን በዚህም ችሎቱ የግራ ቀኙን የቅጣት አስተያየት መርምሮ ተከሳሽ ተከሶ ጥፋተኛ ለተባለበት የወንጀል ህግ አንቀጽ 627(1) በቅጣት አወሳሰን መምርያ ቁ 3/2017 አባሪ አንድ የእስራት ቅጣት እርኬን 40 ላይ ከተመለከተው የቅጣት ሬንጅ ውስጥ ተከሳሽን ያርማል፣ ያስተምራል እንድሁም መሰል አጥፊዎችን ከወድሁ ያስጠነቅቃል በማለት ተከሳሽ በ18 ዓመት ፅኑ እስራት እንድቀጣ ስል ውሳኔ ሰጥቷል።

